(መንግስቱ ጌታሁን)
----የልቤ ጽሕፈት-----
የሚነበብ ቢሆን ልብ እንደ ብራና፣
የተቋጠረውን እፈታልሽና፣
አንቺን ብቻ እንደሚያይ ከሰው ሁሉ አብልጦ፣
ያንቺን ብቻ ስም እንደተጻፈበት በፍቅር ተዳምጦ፣
ሑሉንም እረስቶ ላንቺ እንደሚዋትት፣
አንድ ባንድ ግልጬ የውስጤን ጽሕፈት፣
አሳይሽ ነበረ-
ታነቢው ነበረ-
ፍቅር የተየበውን በነበልባል በእሳት።
....የሚነበብ ቢሆን አይምሮ ተገልጦ፣
የያዘው፡ ያሰበው፡ ይሚወደው በልጦ፤
ያገራችን አበው፡ የቅኔ መርጌታት፡ መፍታት ቢቻላቸው፣
አትሮንስ አድርጌ ያይምሮየን ክታብ አስቀምጬላቸው፣
የቀን አዋዋሌን፡ የሌሊት አዳሬን እያፈራረቁ፣
በፈቱት በወደድሁ በቅኔ በወርቁ።
....
....ፍቀሬ ሆይ ወዳጄ ፥ የልቤ ሰራቂ ርሀቤ ጥሜ፣
እኔማ በፍቅርሽ የፍጥኝ ታስሬ፡ የግድ ተለጉሜ፣
ቀን ሰላም አጥቼ፡
ሌትእንቀልፍ አጥቼ፡
አንቺኑን ተርቤ አንቺን ተጠምቼ፤
ቢርበኝ አልበላ ቢጠማኝ አልጠጣ፣
ሁሌም ስናፍቅሽ፡ ሁሌም ስንገላታ፣
በፍቅርሽ ወላፈን ገላየ ገረጣ።
...ፍቅሬ ሆይ ወዳጄ ፡--
እንደ ሰአሊያኑ ብሩሽን ከቀለም ከሸራ አዋህጄ፣
እንደ ደራሲያኑ፡ በሀሳብ ማዕበል፡ ሞገድ ተወስጄ፣
እንደ ልሂቃኑ ከጥበብ አፍላጋት፡ ልቀዳ ወርጄ፣
....እንደ....እንደ.....ሊቃውንቱ ብያሬድ ዝማሬ አርያም ደርሼ፣
መቋሚያ፡ ጸናጽል፡ ከከበሮ ጋራ፡ ነፍሴን ወደሰማይ በተመስጦ አምጥቄ ፣
ስለፍቅር ልሰብክ አቅሙ ባይኖረኝ፡ እውቀት፡ ወኔ፡ ባጣ፣
ቀን ተሌት ስላንች ሳወራና ሳልም በፍቅርሽ ስቀጣ፤
ለግላጋ ውቨትሽን ብምናቤ ሸራ በተመስጦ ስየው፣
ልቤን ለንጹህ ፍቅር ፍጹም ክፍት አድርጌው፣
ካንቺ ላለኝ ህይወት፡ በሀሳብ ባህር ውስጥ ስቀዝፍ ስዋኝ፣
ቅዝዝ ፍዝዝ ብየ ፍቅርሽን አዝየ እሹሩሩ እንዳልሁኝ፤
ትቢያው ሰውነቴ እያደር ኮስምኖ ቀዝቅዞብኝ ደጄ፣
አንቺን እያሰብሁኝ እዚያው ካለሁበት አለሁኝ ወዳጄ።
.....
እንደ- ሀሳቤማ እንደ ልቤ እውነት፣
ገልጬ ባሳይሽ የልቤን ጽሕፈት፤
አይቻልም እንጂ ቢቻልማ ኖሮ፣
ፈትቼ ባሳይሽ የልቤን ቋጠሮ፤
እንደምን በረካሁ ፌሽታ በሆነልኝ፣
ንጹህ ክቡር ፍቅሬ በፊትሽ ታይቶልኝ።
....ፍቅሬ ሆይ ወዳጄ፡-
ልብ ያሰበውን፡ ድብቅ የውስጥ ስሜት፣
አይምሮ የጻፈውን፡ ህቡዕ ጽሕፈት፣
ከሊቅ እስከ ደቂቅ ርምሮ የሚያውቀው ፣
የሰማዩ ጌታ ኤልሻዳይ ብቻ ነው።
ስለዚህ ምኞቴ መሻቴም እንዲፈጸም፣
እርሱ ይግለጥልሽ፡ የውስጠቴን አለም።
...
ለሰአታት እንኳን ካንቺ ከተለየሁ እስካገኝሽ ድረስ፣
የልብ ምቴ ንሮ ደረቴን ፈንቅሎ ሊወጣ እንደሚደርስ፤
አንዳች ክፉ ነገር የቃዠሁ እንደሆን አንጀት የሚበላ፣
ላጣሽ እየመሰለኝ እንባ እንደሚቀድመኝ ለጭንቀቴ መላ፤
ሁሉን የሚችለው እሱ ይግለጥልሽ ገልጦ እንደብራና፣
እኔማ ድዳ ነኝ፡ ኃይልም ጉልበትም አቅምም የለኝና።
-----------------------------
ይድረሱ ፥
ለ ተወዳጅዋ ባለ ቅኔ
መስከረም 2009 ዓም