ሰኞ 16 ኖቬምበር 2020

ዐምሐራ – ነፃ ህዝብ!

ዐምሐራ – ነፃ ህዝብ!
(ቬሮኒካ መላኩ)

ዛሬ ስለ አማራ ልፅፍ ተነሳሁ ምክንያቴ ደሞ እንደ ራስ ደጀን ተራራ የገዘፈውንና የጠነከረውን የአማራ ስነልቡና እንሰብረዋለን ወይም ሰብረነዋል ብለው የሚያስቡ ደካሞች ካሉ ምኞታቸው ከንቱ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው ። ዘፋኙ “ይሞክሩኛ” እንዳለው አማራን ስነልቡና ይሰበራል ብሎ ማሰብ እና መሞከር እንቁላልን ቋጥኝ ላይ ወርውሮ ነጥሮ ይመለስልኛል ብሎ እንደ ማሰብ የሚቆጠር ነው።



” የወደፊቱን መተንበይ አልፈልግም ፣ ግን አንድ ነገር ብቻ ማለት እፈልጋለሁኝ ።አራት ወራት ሙሉ ከዚህ በአለም ወደር ከማይገኝለት የአማራ ህዝብና ሰራዊት ጋር ስኖር የራሱ የሆነ ከፍተኛ ክብርና ድስፕሊን ያለው መሆኑን እመሰክራለሁ ። ይህ ህዝብ የውጊያ ቅልጥፍና ፣ የዘመቻ ኑሮና የጦር ታክቲኮች ከደሙ ጋር ተዋህደዋል ። ይሄን ህዝብ እግዚአብሄር ይርዳው ። “ አሌክሳንደር ቡላቶቪች ( With the army of Menilik) .

አንባቢዎቼ ረዘም ያለ ፅሁፍ ሊያሰለቻቸው ይችላልና ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባ ። “ስምን መለአክ ያወጣዋል” የሚባል ብሂል አለ ። ለካ ይሄ አባባል ለግለሰብ ስም ብቻ የተባለ ሳይሆን ለህዝብም ነው። በተለይ ለአማራ (አምሃራ) ህዝብ ።
አምሐራ ወይም አማራ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰው ከ 3000 አመታት በፊት ሲሆን” “አምሐራ” የሚለው ስም ከሁለት ቃላት ማለትም “ዐም” እና “ሐራ” የተፈጠረ ነው ።
“ዐም = ሕዝብ ማለት ሲሆን “ሐራ = ነፃ” ማለት ነው ። አምሐራ (አማራ) ማለት “ነፃ ህዝብ ” ማለት መሆኑን የተለያዩ የታሪክ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል ።

የአማራ ህዝብ የስሙ ትርጓሜ እንደሚያመለክቱት ነጻነት በገንዘብ የማይተምኑት፣ በስጦታ የማይደለሉለት የሰው ልጅ ፍላጎት ነው ብሎ በፅኑ ያምናል። ድህነት፣ ማጣት፣ ችግርና የመሰለው ምንም አይነት መከራ ቢመጣ አማራዎች ነጻነትን ለድርድር እንዲያቀርቡ አያደርጋቸውም። ነጻነት ክብር ነው፤ ክብር ደግሞ በምድር ላይ ለሰው ልጅ የተሰጠ ጸጋ ነው። ይህን ደግሞ ከምንም ከማንም በላይ አማሮች ያውቁታል።ለዘመናት ከጠላቶቹ ጋር ሲዋጋ ግንባሩ ታጥፎ የማያውቀው ጦረኛው የአማራ ህዝብ በነፃነቱ ድርድር እንደማያውቅ አስመስክሯል ።

ታሪክ ምስክር ነውና የአማራን ህዝብ የነፃነት እና የአይበገሬነት ስነልቡና እየነቀስን እንተርከው ። በ 19ኛው ክዘ አጋማሽ ላይ ለአፍሪካ የወደፊት እድል ወሳኝነት ያላቸው ሁኔታዎች በመከሰት ላይ ነበሩ ። በዚህ አንገብጋቢ ወቅት አፍሪካ በነጮች ተከፋፍላ ስትያዝ በብቸኝነት ነፃነቷን ያስከበረችው አገር ኢትዮጵያ ነበረች ። በዚህ የኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክ ውስጥ የአማራ ህዝብ የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ የአገሩን ነፃነት አስከብሯል ። በዚህ ወቅት ነበር እንግድህ የተለያዩ የምእራባውያን ፖሊሲ አውጭዎች “የአማራ ህዝብ ካልጠፋ ወይም የነፃነት ስነልቡናው ካልተሰበረ ኢትዮጵያን መጠቅለል አይቻልም” በማለት የደመደሙት።
በ 1930 ዎቹ በአዲስ አበባ ተመድቦ የነበረው የምእራባውያን ወኪል የነበረው ባሮን ሮማን ፕሮችዝካ ለአውሮፓውያን ባቀረበው ሪፖርቱ እንድህ በማለት ገልፆት ነበር :…

“አውሮፓውያን መንግስታት ልብ ብላችሁ ስሙኝ። በምሳራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አማራ የተባለው ህዝብ በፍጥነት መፍትሄ ካልፈለግንለት ለአውሮፓውያን ህዝቦች ከፍተኛ አደጋ ነው። በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የእኛ የነጭ ዘሮችን ፍላጎት ካለምንም ችግር ለማሳካት ከተፈለገ በአማራ ላይ የምንከተለው ፖሊሲ ማውጣት አለብን።” የሚል ሪፖርት ለአውሮፓ መንግስታትና ለአሜሪካው የመረጃ ድርጅት ልኳል።

ባሮን ሮማን ፕሮችዝካ ( Abyssinia the powder Barrel , Publisher British International news Agency 1936)።
ሌላው ለዘመናት የአማራ ህዝብን የነፃነት ስነልቡና ለመስበር አውሮፓውያን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንና ያደርጉ እንደነበር የሚያሳየን መረጃ የሚገኘው ከታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ስባኪ መፅሃፍ ነው ።
አልቤርቶ ሰባኪ Ethiopian under Mussoloni and Fascist experience በሚል ርእስ በፃፈው መፅሃፉ እንደሚከተለው ይላል :…

“ኢትዮጵያን በኢጣልያ መያዝ ለማፋጠን ሲሉ ኢጣልያኖች የውስጥ ቅራኔንና ጥላቻንና ግጭትን ለማባባስ አማራ ያልሆኑ ጎሳዋችን በማሳመፅ ለመጠቀም ብዙ ሞክረዋል ።”
መፅሃፉ ይቀጥልና መጀመሪያውኑ ኢጣልያ ከአማሮች ተቃውሞ እንደሚኖር ጠብቀዋል ። ለዚህ የኢጣልያ ስጋት አንዱ ምክንያት አማሮች አላቸው የሚባለው የወታደራዊ ጀግንነት ታሪክ ነው ።
ግራዚያኒ …… “አማሮች ምንም እንኳን ለጊዜው ያመኑ ቢመስሉም አመች ጊዜ መርጠው ለማጥቃት አድብተው ይጠባበቃሉ” በማለት የየአካባቢው ገዥወች አማሮችን እንዳጠፉ መመሪያ ሰጥቷል። ይሄ ሁሉ ግፍ በአማራ ላይ ተፈፅሞበት የአማራ ህዝብ ስነልቡና ጢም እንዳለ ነበር። ይሄን የነፃነት ስነልቡና ፈፅሞ መስበር አልቻሉም ።

አልቤርቶ ስባኪ ይቀጥላል

ኢጣልያኖች አማሮችን በኦሮሞዎች ፊት ለማሰቃየት ቢሞክሩም እንኳን ጥቂቶች አማሮች በነበራቸው የፖለቲካ ብስለት የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ችለዋል። እንደ እውነቱ አማሮች ችላ ሊባሉ የሚችሉ ሰዎች አልነበሩም። በነበረባቸው ተፅእኖ ሳይዳከ መንፈሰ ጠንካሮች ሆነው በህብረተሰቡ ውሥጥ የነበራቸውን እንዳለ ለማቆየት ችለዋል።
ሌሶና ኢትዮጵያን በጠቅላይ ግዛት ሲያዋቅር አማሮችን በመንግስት መስሪያ ቤቶች መቅጠር ከልክሎ ነበር (ወያኔም የሌሶናን ፖሊሲ ተከትላለች)።

ኢጣልያኖች አማሮችን ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ቅራኔ ውስጥ በማሥገባትና ፀረ አማራ ፖሊሲ በመከተል በመከተል በራሳቸው ላይ ተቃውሞ አጠናክረዋል።” እያለ የዚህን ተአምረኛ ህዝብ አይበገሬነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገር ዘንድ ከትቦት አልፏል።
የፋሽስት ሙሶሎኒን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሸምድዶ በኢትዮጵያ ላይ የተገበረው አምባገነኑ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም፡

 በአንድ ወቅት

“ኦርቶዶክስንና አማራን ካላጠፋን መሪት ትክበዳቸውና መቸም አገሪቷን በምንፈልገው መንገድ መምራት አንችልም።” በማለት የአማራን አይበገሬነት ተንፍሶ ፍግም ብሏል። ይሄ የመለስ ንግግር ከባሮን ሮማን ፕሮችዝካ እና ሩዶልፍ ግራዚያኒ ስለ አማራ ከተናገሩት የተኮረጀ እንደነበር በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

አሁን ወደ ፅሁፌ መደምደሚያ እየደረስኩኝ ነው። የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ከአራት ሺ በላይ ዓመታት ባስቆጠረው ያልተቋረጠ ረዥም ታሪኩ በርካታ የጨለማ እና የብርሃን ዘመናትን አሳልፏል። ብዙ ጊዜ ወድቆ ተነስቷል። አለቀለት ሲባል አገግሟል። ጠላቶቹ ቀብረነዋል ሲሉ ነፍስ ዘርቷል። ያን ሁሉ ዘመን በውጣ ውረድ ሲያሳልፍ አንድም ቀን ለአንድም ሰከንድ የስነልቡና መውደቅ አጋጥሞት አያውቅም። እንደውም ለሌሎች መሰል ህዝቦች በአርአያነት የሚጠቀስ የአይበገሬ ስነልቡና ተምሳሌት ሆኗል።
አማራ ድሮም በፋሽስት ጣሊያን ዛሬም በፋሽስት ወያኔ በደል ቢደርስበትም ሚስማር ሲመቱት እንዲጠነክር በደሉ የህዝቡን ወኔ ይባስ ቀሰቀሰው እንጂ ወደኋላ አልመለሰውም።
ተስፋ ሊያስቆርጡ የሚችሉ እጅግ በርካታ ምክንያቶች ቢደረደሩም ክብርና ነጻነትን ማቆየት ግን ከሁሉ በልጠው አመዘኑ። የአማራ አይበገሬ ስነልቡና እንደ አልማዝ አንፀባራቂና የማይሰበር ሆኖ ወጣ ።

ዛሬስ?

ዛሬም ቋንቋ ያልተደባለቀባቸው፣ ቀለማቸው ያልደበዘዘ ባቸው፣ ባህል ያልተሰወረባቸው፣ ውበታቸው ያልተበረዘባቸው የራሳቸው ማንነት ያልጠፋቸው ልጆቻቸው ያለአንዳች ሃፍረት አንገታቸውን አቅንተው በኩራት እንዲቆሙ ሆነዋል። እነዛ ብርቱ አማሮች የኢትዮጵያዊ መልክ ይቀየር ዘንድ ለጠላት እጅ አልሰጡም፤ አልፈቀዱምና። እንደ ስማቸው ነፃ ህዝቦች ናቸውና ። እመኑኝ! ይህቺ በደም የቆየች የአማራ የነፃነት አይበገሬ ስነልቡና መቼም አትሰበርም ።
ታሪክ ሙት አይደለም።አይሞትም።ታሪክ የሚሞተው በታሪክ ሰሪው ትውልድም ሆነ በተከታዮቹ በወጉ ተመዝግቦ ሳይቀርብና ተረካቢ ትውልድ ሲያጣ ብቻ ነው። የአማራ ህዝብ ታሪክ ደሞ ትናንትም በአባቶቻችን ቀለም ተበጥብጦ ብራና ተፍቆ ዛሬም በውድ ልጆቻቸው ዘመኑ በሚፈቅደው ላይጠፋ ከዘመን ወደ ዘመን ሊሸጋገር ተከትቧል ። አኩሪ ታሪካችን የጠንካራው ስነልቡናችን አንዱ ምንጭ ነው ። የአማራ ታሪክ እና ስነልቡና ሁሌም ዘመን ተሻጋሪ ነው።

የአፄ ቴዎድሮስ ፍርዶች


የአፄ ቴዎድሮስ ፍርዶች 

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)
  • አፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ፀሐፊያን ፍርድ አዋቂም ፍርድ ገምድልም ነበሩ ይሏቸዋል። 
  • ይህን አባባላቸውን የሚያሳዩ አፄ ቴዎድሮስ እንደሰጧቸው... በታሪክ ፀሐፊዎች የተፃፈ ፍርዶች
  • የዘመኑን የፍትህ ስርዓትና ህብረተሰቡ ለፍትህ የነበረውን አመለካከትና የፍትህ ባህል የሚያሳዩ ፍርዶች
  • ንጉሱ ራሳቸውን ጥፋተኛ ያሉበትና ተከሳሽ ሆነው የቆሙባቸው ክርክሮች እና ሌሎችም አፄ ቴዎድሮስ ስለሰጧቸው የተለያዩ ፍርዶች ነው። 
ካሳ ኃይሉ በ1811 ዓ.ም ጥር 6 ቀን ተወለዱ። በ1845 የካቲት ወር አፄ ቴዎድሮስ ተብለው ነግሰው እስከ 1860 ከእንግሊዝ ጦር ጋር መቅደላ አምባ ላይ በተደረገው ውጊያ ጦራቸው ስለተሸነፈ በገዛ ሽጉጣቸው እራሳቸውን ገድለዋል። አፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ስያሜያቸው ቴዎድሮስ እንዲሆን የመረጡት “ቴዎድሮስ የሚባል ንጉሥ ሲነግስ ኢትዮጵያን እስከ ባህር ያሰፋታል ፍርድና አስተዳደርንም ያስተካክላል” የሚባል ትንቢት ስለነበር ሕዝቡ “ይህ ትንቢት የእርስዎ ነው” እያሉ አሞካሿቸው። ስሜን ቴዎድሮስ በሉ ብለው አወጁ ይለናል ታሪካቸውን ፅፎ በ1985 ያሳተመው ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ።ጳውሎስ “ቴዎድሮስ እንዴት ያሉ ሰው ነበሩ” የሚለውን ጥያቄ በመፅሐፍ አንስቶ “ሁሉንም ጠባይ አሟልተው የያዙ ሰው ነበሩ። ይህም ማለት ደግ ናቸው፣ ክፉም ናቸው፣ ሩህሩህ ናቸው፣ ጨካኝም ናቸው፣ ፍርድ አዋቂ ናቸው፣ ፍርድ ገምድልም ናቸው” ሲል ማስረጃ እያጣቀሰ ይገልፃቸዋል። እኛም ዛሬ ጳውሎስ ኞኞ በመፅሐፍ ላይ ያስፈራቸውን የአፄ ቴዎድሮስን ፍርዶች እንመለከትና በዘመኑ የነበረውን የፍትህ ስርዓት በመጠኑ እንቃኛለን። በሰጧቸው ፍርዶች መነሻነትም በትንቢት ተነግሮላቸዋል። እንደተባለው ፍርድና አስተዳደርን በማስተካከል ረገድ ምን ያህል ተሳክቶላቸው ነበር የሚለውን የራሳችንን ግንዛቤ እንይዛለን። ፍርዶቹ አንዳንዶቹ አስገራሚ፣ አንዳንዶቹ አሳዛኝና አስደንጋጭ አንዳንዶቹም አስተማሪ ናቸው። ለማንኛውም እንቀጥል. . .

 1. የጋይንቱ ችሎት

አፄ ቴዎድሮ ጎንደር ጋይንት ላይ ሰፍረው ሰለ ወታደሮቻቸው በአርሶ አደሩ ላይ ተሰሪ አገቡአቸው። ተሰሪ ማግባት ማለት አርሶ አደሩ ወታደሮቹን እንዲቀልብ በየቤቱ መመደብ ማለት ነው። በወቅቱ የተደራጀ ጦር ሰራዊትና ለጦር ሰራዊቱ የሚመደብ የመንግሥት ባጀት ስላልነበር የነገስታቱ ጦር በየደረሰበት ያለው ህዝብ እንዲቀልበው ይታዘዝ ነበር። ከእነኚህ የጋይንት እና የአካባቢው አርሶ አደር እንዲቀልባቸው ከታዘዘላቸው የቴዎድሮስ ወታደሮች መሀል አንዱ ወታደር አንዱን አርሶ አደር ገደለው። የሟች ዘመዶች ለአፄ ቴዎድሮስ አመለከቱ። አፄውም ወታደሮቻቸውን አፈርሳታ አስቀምጠው ገዳዩን እንዲጠቁሙ አዘዙ። ሆኖም ወታደሮቹ በሙሉ በአንድ ላይ አድመው ገዳዩን አናውቅም ብለው በቄስ እየተገዘቱ ስለወጡ ገዳዩ ሊታወቅ አልቻለም። ቴዎድሮስ ገዳዩን ወታደር ለማወቅ የተደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ተናደው “ወታደር ብላ ባላገር አብላ ያልኩ እኔ ነኝ። ደመኛህም እኔ ነኝና እኔን ግደል” ብለው ተነስተው ለከሳሽ ነገሩት። ከሳሽም ምኑ ሞኝ “እኔ ንጉስ መግደል አይቻለኝም” አለ። ቴዎድሮስ እንግዲያውስ ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም ብለው ለሟች ወገኖች የደም ካሳ ገንዘብ ከፍለው አሰናበቷቸው።

2.  የንጉሱ ትዕዛዝ

በአስቸኳይ ተልኬ ነው ልለፍ” አለው። የፈርቃ በር ጠባቂም “ከንጉሥ ከተላክ አትከልክሉት ይለፍ የሚል በማህተም የተደገፈ የይለፍ ደብዳቤ ካለህ አሳየኝ እና አሳልፍሃለሁ ካልሆነ ግን እኔም የንጉሥ ትዕዛዝ ስላለብኝ አታልፈም” ሲል መለሰለት። መልዕክተኛው ወታደርም የንጉሥ ትዛዝ ሆኖበት በግድ አልፋለሁ ብሎ መንገድ ሲጀምር ጠባቂው ወታደር በጥይት ተኩሶ ገደለው። የሟቹ መልዕክተኛ ወገኖችም ጉዳዩን ከሰሱና ለፍርድ አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀረቡ። 

በችሎት የተቀመጡት ፈራጆች ሁሉ ገዳይ ላይ ፈረዱ “እምቢ አልፋለሁ ቢልህ ለንጉሥ ማመልከት ሲኖርብህ እንዴት የንጉሥ መልዕክተኛ ትገላለህ ለጥፋትህ ሞት ይገባሃል” ሲሉ ፈረዱበት። አንድ አስተዋይ ፈራጅ ከተቀመጡበት ተነስተው “መታየት የሚገባው ከንጉሡ የተሰጠው ትዕዛዝ ነው። ንጉሡ የፈርቃ በር ጠባቂን ጠርተው ያለኔ ፈቃድ እርጉዝ ሴት እንኳን እንዳታልፍ ብለው አዘዙ። መልዕክተኛውን ደግሞ በአስቸኳይ የጁ ደርሶ እንዲመጣ በማዘዛቸው በዚያ በፈርቃ በር በኩል ማለፍ ነበረበት። ስለዚህ ጥፋቱ የሚመለከተው ንጉሥ ነገስቱን ነው። ነገር ግን ብርሃን ናቸውና ምን ይደረግ” ብለው ተቀመጡ። እዚህ ጋር እንግዲህ በዚያ ዘመን የነበረውን ንጉሥ የሚያስተች ዲሞክራሲ ሳናደንቅ አናልፍም። የአስተዋዩ ፈራጅ ንግግር ብቻ ሳይሆን የንጉሡም ምላሽ የሚደንቅ ነው። አፄው ምን አሉ መሰላችሁ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው “እንዲህ ነው መሸምገል፣ ሁለት ጠጉር ማብቀል” ብለው የአስተዋዩን ፈራጅ ፍርድ ካደነቁ በኋላ “በደለኛው እኔ ነኝ ፍረዱብኝ” ብለው በተከሳሹ ወታደር ቦታ ወርደው ቆሙ። ከዛም ፈራጆች በሰጡት ፍርድ መሰረት ለሟች ወገኖች 500 ብር የደም ካሳ እንዲከፍሉ አፄ ቴዎደሮስ ላይ ፈረዱና ጉዳዩ በዚህ ተቋጨ።

ቴዎድሮስ ለአንድ ታማኝ ወታደራቸው ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፈው “በፈርቃ በር በኩል እርጉዝ ሴት እንኳን ብትሆን እንዳታልፍ ጠንክረህ ጠብቅ” አሉት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ሌላውን ወታደራቸውን ጠርተው “ፈረስ እያለዋወጥክ ይህን ወረቀት የጁ አድርሰህ በስድስት ቀን ውስጥ በአስቸኳይ ተመለስ” ብለው አዘዙ። መልክተኛው ወታደር መልክቱን ለማድረስ ፈርቃ በር በሚባለው ቦታ ማለፍ ግድ ሆነበት። ፈረሱን እየጋለበ ፈርቃ በር ደረሰ። አስቀድሞ ማንንም እንዳያሳልፍ የታዘዘው የፈርቃ በር ዘበናም የንጉሱን መልዕክት እንዳያልፍ ከለከለው። መልዕክተናው “ከንጉሡ በስድስት ቀን የጁ ደርሼ እንድመለስ

3. በቴዎድሮስ አምላክ!

በወቅቱ ንጉሥ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ሕግም ነበር። ‘በንጉሥ አምላክ' ከተባለ አሁን በሕግ አምላክ ከሚባው በላይ ማንኛውም
ድርጊት ይቆም ነበር። ይሄ ታሪክም ከዚሁ ጋር ይያያዛል አንድ ሌባ ከአንድ ሀብታም ሰው ቤት ሌሊት ለስርቆት ገብቶ በረቱን ሲያንጎዳጉድ ባለቤቱ ከእንቅልፍ ነቅቶ መጣበት። ባለቤት ሲያባርር ሌባ እግሬ አውጪኝ ፈረጠጠ እንደማይደርስበት የገባው
ባለቤት። “በቴዎድሮስ አምላክ ቁም” ብሎ ሌባውን አወገዘው ሌባውም በቴዎድሮስ አምላክ መባሉን ሲሰማ ቆሞ ጠበቀው። ሀብታሙ ሰውም ሌባውን በያዘው ጦር ደጋግሞ ወግቶት ጥሎት ሄደ። ሌባው አልሞተምና በአቅራቢያው ወዳለው የአርዋ ሚካኤል ቤ/ ክርስቲያን ገብቶ እስኪያገግም ቆየ። 

አፄ ቴዎድሮስ እንፍራንዝ መጥተው መስፈራቸውን ሲሰማም እያዘገመ ሄዶ ታሪኩን ነገራቸው። ቴዎድሮስም በጥሞና ካዳመጡት በኋላ “አንተ የሌሊት ጅብ ከሰው በረት ምን ልታደርግ ገባህ? አበጀ ደግ አረገህ ብለው ሌባውን አስደነገጡትና ሀብታሙ ሰው ተይዞ እንዲመጣ አዘዙ። ሀብታሙ ሰው እንደመጣ አፄው በፈገግታ “እህሳ አንተ ጎበዝ ይህን ሌባ እንዴት ወጋኸው?” ብለው እየሳቁ ጠየቁት። ሰውዬውም በደስታ “በረቴን ከፍቶ ገብቶ ከብቶቼን ሊነዳ ሲል ነቃሁና ምዝራጤን (አንካሳዬን) ይዤ ልወጋውስል ኮቴዬን ሰምቶ አብላክ አለ (ሮጠ) እኔም ተከትዬው እንደማልደርስበት ሳውቅ በቴዎድሮስ አምላክ ብለው መሮጡን ትቶ ቀጥ ብሎ ቆመልኝ እንደደረስኩም በያዝኩት አንካሴ ወደወድኩት (ወጋሁት) ብሎ ነገራቸው። ቴዎድሮስ የሰውየውን ንግግር ሰምተው እንደጨረሱ “ወንጀለኛ ነህ እንዴት በስሜ ቆሞልህ ትገድለዋለህ። መሞት ይገባህ ነበር። ግን ምሬሃለሁና ያለህን ሀብትና ንብረት በሙሉ ለወጋኸው ትለቃለህ” ብለው ፈረዱበት።

4. ባለ ወይፈኗ

አንዲት አንድ ወይፈን ብቻ ትቶለት በበሬ ባሏ የሞተባት ሴት ነበረች። ያላት ብቸኛ ንብረት ወይፈኑ ነበርና ቤቷን የምታስተዳድረው በዚሁ ወይፈን በምታርሰው መሬት ነበር። ሆኖም ግን ወይፈኑ ሴት ከብት ፍለጋ እየዞረ አላርስ ብሎ አስቸገራት። የመንደሩን ሰዎች እንዲኮላሹላት ብትለምናቸውም ወይፈኑ ጥሩ ቁመና የነበረው ምርጥ ዝርያ ያለው ስለነበር ከብቶቻቸውን እያጠቃ ጥሩ ዝርያ ያለው ጥጃ ስለሚያስወልዳቸው ለጥቅማቸው ሲሉ እምቢ አሏት። ወይፈኑም እርሻ እምቢ ብሎ ለግሞ እየዞረ የመንደሩን ሰዎች ከብቶች ሲያስወልድ ከረመ። አንድ ቀን ወይፈኑ ከአንድ በሬ ጋር ሲዋጋ ጉልበተኛ ነበርና በሬውን ገፍቶ ገደል ከተተውና በሬው ተሰባብሮ ሞተ። ይሄኔ የሞተው የበሬ ባለቤት ባለወይፈኗን “ተዋጊ በሬህን ተናካሽ ውሻህን ያዝ ያላልና ሕጉ የበሬውን ዋጋ ክፈይኝ” ሲል ከሰሳት። 

ባለወይፈኗ በየደረጃው በሽማግሌም ሆነ በዳኞች የበሬውን ዋጋ እንድትከፍል ፈረዱባት። ኢትዮጵያውያን በጥንትም ታሪካችን በፍትህ እናምናለን ከፈጣሪ በታች የመጨረሻው የዳኝነት ሰጪ እስከሆነው እስከ ንጉሡ ችሎት ድረስ ፍትህን ለማግኘት ከታች ከአጥቢያ ዳኛ ተነስተው ከብቶችና መሬታቸውን ሸጠው ጥሪታቸውን አሟጠው የንጉሡ መናገሻ ድረስ ይግባኛቸውን ይዘው የክርክሩ መነሻ ትንሽም ይሁን ትልቅ ለዓመታት ተስፋ ሳይቆርጡ እንደሚሟገቱ የህጎቻችንን ታሪኮች የፃፉ ምሁራን ከትበውታል። እንዲያውም “ያለ ፍትህ ከተወሰደች አንዲት ዶሮ እና በፍትህ በመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ከተወሰደች አንዲት በቅሎ ያለፍትህ የሄደችው ዶሮ ታስቆጫለች” የሚለው ነበር። ብሒል የበለጠ ለፍትህ ያለንን ቀናኢነት እና የፍትህ ባህላችንን የሚያሳይ ነው። ይህ ከሚያኮሩን በርካታ ባህሎችና አመለካቶች አንዱ ሆኖ መጠቀስ አለበት። 

ባለወይፈኗም በዚሁ የፍትህ ባህላችን መሰረት ከአፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀርባ በበታች ዳኞች በተወሰነባት ፍርድ የተሰማትን ቅሬታ አሰማች። አፄ ቴዎድሮስም ጉዳይዋን በጥሞና ከሰሙ በኋላ “ሕጉ ያዛልና ወይፈንሽ የገደለውን ዛሬ ዋጋ መክፈሉንስ ትከፍያለሽ” ሲሉ ፈረዱ። ነገር ግን አንድ ጥያቄ ጠየቋት፡፤ “ለመሆኑ ለዚህ ወይፈንሽ የተወለዱትን ከብቶች ታውቂያቸዋለሽ?” አሏት “አዎን ንጉሥ ሆይ አውቃቸዋለሁ” ስትል መለሰች ባለወይፈኗ አፄ ቴዎድሮስም አጋፋሪያቸውን ጠርተው “ንሳማ እሷ የምታሳይህን ከብቶች ሁሉ እየያዝክ አንድ ለሷ አንድ ለባለ ላም እየደረክ አካፍላቸው” ብለው አዘዙ። አፄ ቴዎድሮስ ወይፈኗ ያደረሰውን ጉዳት እንድትከፍል ብቻ ሳይሆን ካስገኘው ጥምም እንድትጋራ ስለፈረዱላት ሴትዬዋ በተከፈለቻቸው ከወይፈኗ የተወለዱ ከብቶች በአንድ ጊዜ ሀብታም ሆነች።

5. አርባ ክንድ መቀነት

አንዲት ሴት አርባ ክንድ ያለው መቀነት አሰርታ ለአፄ ቴዎድስሮ ስጦታ ሰጠች። አፄውም ስጦታውን ተቀብለው “እንዴት በአርባ ክንድ መቀነት ወሰንሽኝ እንደተራሰው ቆጥረሺኝ ነው?” ቢሏት። ሴትየዋም “አይደለም ጃንሆይ ድሃ ብሆን ነው እንጂ ለእርስዎስ መቶ ክንድም አይበቃም” ስትል መለሰች። በመልሷ የተደሰቱት ንጉሥም ሴትየዋን ሸልመው አሰናበቷት፡፤ ይህን የሴትየዋን ታሪክ የሰማች ሌላ ሴት ለዚያች ለመልከ ጥፉ ያን ያህል የሸለሙ የኔንማ ቁንጅና ሲያዩ የበለጠ ይሸልሙኛል ብላ ከአፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀርባ እጅ ነሳች። አፄ ቴዎድሮስም “ሙያሽ ምንድን ነው እቱ?” ብለው ጠየቋት። ሴትየዋም “የከተማ ቅሬ (ሴተኛ አዳሪ) ነኝ እንጂ ሌላ ስራ የለኝም ብላ መለሰችላቸው።

አፄ ቴዎድሮስም ሴትዬዋ ስራፈትነትን የምታበረታታ ሙያ የሌላት ስርታ የላቧን ከማግኘት ይልቅ በአስነዋሪ የዝሙት አዳሪነት
ተግባር ላይ መስማራቷንና አስባ የአቅሟን የመቀነት ስጦታ ያቀረበችውን ታታሪ ሴት ለፍታ ያገኘችውን እሷ በከንቱ ለማግኘት
መምጧን ሰለተረዱ እንዲህ ፈረዱባት። “እግዚአብሔር ሁለት እጆች የፈጠረልሽ እንድትሰሪባቸው ነበር። ለመብል ብቻ ከሆነ ግን አንድ እጅ ይበቃሻል” ብለው ለመሰሎችዋ መቀጣጫ እንድትሆን አንድ እጇን አስቆርጠው ቀጧት። የዘመኑ አዝማሪዎች በዚህች ሴት ላይ የደረሰውን ቅጣት ታዝበው የዘፈኑትን ግጥም ለአፄ ቴዎድሮስ ፍርዶች መቋጫ አርገን እንድሰነባበት። የዘመኑ አዝማሪዎች እንዲህ ሲሉ ዘፈኑ
“ማረስ ይሻላል መገበር
እጅ እግርን ይዞ ለመኖር
አላርስም ያሉ አልነግድ
ተመለመሉ እንደ ግንድ”

ዐምሐራ – ነፃ ህዝብ!